“አንድ መጽሃፍ ለአንድ ተማሪ” ዘመቻ ሪፖርት

“አንድ መጽሃፍ ለአንድ ተማሪ” ዘመቻ ሪፖርት
የጣና ሃይቅ ት/ቤትን ቤተ-መጻህፍት ካለበት የመጽሃፍ ዕጥረት ለመታደግ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ “አንድ መጽሃፍ ለአንድ ተማሪ” በሚል የድጋፍ ዘመቻ ማድረጋችን ያታወቃል። የቀድሞ ተማሪዎችና ባለቅን ልባም የትምህርት ቤቱ ደጋፊዎች ያደረጋችሁት በጎ ተግባር በመደጋገፍ ምን ያህል አኩሪ ስራ መስራት እንደሚቻል አስይታችኋልና አምላክ ይባርካችሁ!በዚህ ዘመቻ የተሳተፋችሁ፤ እንዲሁም ጊዜአችሁን ሰጥታችሁ ያስተባበራችሁ በሙሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ!
በአጠቃላይ 629 መጻህፍት እስካሁን ተሰብስቧል። ከዚህ ውስጥ 288ቱ ለ9ና10ኛ ተማሪዎች የሚሆኑ አጋዥ መጻህፍት ሲሆኑ፤ ቀሪው 341 መጻህፍት ደግሞ የ11ና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚያግዝ ነው።
ዘመቻው ይቀጥላል። ሁላችንም እንሳተፍ! ትውልድ እንታደግ! ጣና ሃይቅ ት/ቤት ከ3,500 በላይ ተማሪዎች አሉት። በቤተ-መጻህፍቱ ውስጥ ያሉት መጻህፍት ግን እንኳን ለዚህ ሁሉ ተማሪ ለአንድ ክፍል ተማሪዎች እንኳን የማይመጥን ነው። እኛ ከተባብርን ግን ቤተ-መጻህፍቱ በመጻህፍት
መሙላት እንችላለን። በአጋዥ መጻህፍት እጥረት ተማሪዎች ከቤተ-መጻህፍት እንዳይርቁ ማድረግ እንችላለን።

 

የጣና ሃይቅ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት

“አንድ መጽሃፍ ለአንድ ተማሪ” ዘመቻ

ከሀገር ውጪና በሀገር ውስጥ የምንኖር የቀድሞ የጣና ሐይቅ ተማሪዎች “የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረትን” (Tana Haik Alumni Network) አቋቁመን ለጣና ሐይቅ ት/ቤትና ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡

ኤደን መታፈሪያ Eden Metaferia የጣና ሃይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት አባል ናት። ኤደን ኑሮዋ በስዊድን ቢሆንም የጣና ሃይቅ ት/ቤትን ችግሮችን አይታ ህሊናዋ ሊያርፍ አልቻለም። ከ3500 ተማሪዎች በላይ የያዘው ይህ ት/ቤት በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት መጽሃፍት የያዘ ላይብራሪ ነው ያለው። እንዴት ነው በዚህ መልክ ትውልድ መቅረጽ የሚቻለው? እንዴትስ ተማሪዎች ላይብራሪ ሊዉሉ ይችላሉ? ይህ እረፍት ነስቷት “አንድ ሰው አንድ መጽሃፍ” ቢሰጥ ላይብራሪውን በቀላሉ መሙላት ይቻላል በማለት ይህን ለማስተባበር ከስዊድን ባህርዳር ገብታለች። እንዴት አይነት ቅን ልቦና አስተዋይነት ነው ይሄን ያህል ርቀት የሚያስመጣና “ኑ በጋራ ለተማሪዎች እንድረስላቸው” የሚያስብል ህሊና?

እኛ ደሞ “አዎ ይቻላል፤ አናግዝሽና ተባብረን ላይበራሪውን በመጽሃፍ እንሙላው” እስቲ እንበላት! ለታናናሽ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እስቲ እንድረስላቸው! “50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ነው፤ ለሃምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው” አይደል ሚባለው! አንድ አንድ መጽሃፍ (አዲስ ወይም ያገለገለ)እስቲ ሁላችንም እናዋጣ!
ተማሪዎች የሚፈልጉትን መጽሃፍት ዝርዝር ጠይቀናል። ከዚህ ጽሁፍ ስር ተዘርዝሯል።

በሉ አሁኑኑ አንድ አንድ መጽሃፍ እየያዛችሁ (ከአንድ በላይም ማበርከት ይቻላል) ታየ ሞላ ስቴሽንሪ ሄዳችሁ አስቀምጡ (የተቀመጠው ፎርም ላይ ስማችሁንና የመጽሃፉን ስም ጻፉ)።

ተጨማሪ መጽሃፍ ማስቀመጫ ቦታዎችን ነገ እናሳውቃችኋን። ከባህርዳር ከተማ ርቃችሁ ለምትገኙ የት/ቤቱን ፖስታ ሳጥን ቁጥር እናሳውቃችኋለን።

ሁላቸንም እንሳተፍ – አንድ ሰው አንድ መጽሃፍ ማዋጣት አያቅተውም!

ተማሪዎች የሚፈልጓቸው የመጽሃፍት ዝርዝር ከዚህ በታች አለላችሁ።

 

“ኑ ትውልድን በእውቀት እናንፅ”

 

ከአብሮት ሰላምታ ጋር

የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረት

Tana Haik Alumni Network (THAN)