በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የተመሰረተው ወንፈል ተራድዖ (Wonfel Aid) የተባለው ድርጅት የዚህን ዓመት ትልቁን ስጦታ በጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ሕብረት በየዓመቱ ለሚካሄደው የጣና ቤተሰብ ስኮላርሺፕ ገቢ ማሰባሰቢያ አበርክቷል፡፡
ወንፈል “የተሰጠንን እንሰጣለን” በሚል መሪ ቃል የተቋቋመ ሲሆን በዋናነት በኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና የአደጋ ጊዜ እርዳታዎች ላይ አተኩሮ ያለትርፍ የሚሰራ ግብረ ሠናይ ድርጅት ነው፡፡
ታዳጊ ተማሪዎችን በማገዝና በተለይም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁ እንዲሆኑ ልዩ የተግባር ስልጠና በመስጠትም ይታወቃል፡፡ በጦርነት ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በማሳደግ፣ የተፈናቀሉ እናቶችን በማቋቋም ከፍተኛ ስራዎችን በመስራት ይገኛል።
በዚህ ፈታኝ ወቅት በባህር ዳር ጣና ሃይቅ የሚገኙ ታዳጊ ተማሪዎቹን ለማገዝ ወንፈል ላበረከተው የ2500 ዶላር ስጦታ የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ሕብረት ከልብ የሆነ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
ለተጨማሪ መረጃና ተሳትፎ ድረ-ገፁን እንዲጎበኙ እንጋብዛለን፡

የጣና ቤተሰብ ስኮላርሺፕ (TFS) በላቀ የትምህርት ውጤታቸውና በቤተሰብ ገቢ ሁኔታቸው የተመረጡ ታዳጊ ተማሪዎችን ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ፣ ሴት ተማሪዎችን በልዩ ሁኔታ የሚያበረታታና ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችም እገዛ የሚያደርግ ፕሮግራም ነው።
ላለፉት ስምንት ዓመታት ባካሄዳቸው ስምንት የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሮች፡ ከቀድሞ የጣና ሐይቅ ተማሪዎች እና ደጋፊዎች በተደረገ ድጋፍ፦
- ከ232 በላይ ተማሪዎችን በየወሩ በወጪ ደግፏል።
- ከ2100 በላይ ለሆኑ ሴት ተማሪዎች ወርሃዊ ንጽህና መጠበቂያ በየወሩ አቅርቧል።
- ከ40 በላይ ዓይነስውራን ተማሪዎችን የሚያግዙ ድምፅ መቅጃዎችን አቅርቧል።
- ወደ ዩንቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች የዝግጅት ወጪን ሸፍኗል።
- የኮምፒውተር ላብራቶሪዎችን የኔትወርክና ኤሌክትሪክ ዝርጋታ በባለሙያ አሥሰርቷል።
- ለሴት ተማሪዎች መፀዳጃ ቤት ሥራ የገንዘብና የማማከር ድጋፍ አድርጓል።
- እንዲሁም የመምህራን ማረፊያ ክፍል እድሳት እና አዲስ ሎከሮችን አዘጋጅቷል።
- የቤተመጽሐፍት ወንበሮች ድጋፍና የመጠጥ ውሃ ማጠራቀሚያ (water tank) አቅርቧል።
በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት የመጽሐፍ ማሰባሰብና የፅዳት ዘመቻዎችን አስተባብሯል። ሁሉም ሥራዎች የተሳኩት ግን ይህን በጎ ዓላማ ሰምተው በደገፉ ብዙ የተባበሩ እጆች እንደሆነ እናምናለን።
ባለፉት ዙሮች በነበረው ተሳትፎ ከቀድሞ ተማሪዎች በተጨማሪ ሁሉም በጎ አሳቢ ኢትዮጵያውያንና ጉዳዩን ከወዳጆቻቸው የሰሙ የውጭ ሀገር ዜጎችም ጭምር መሳተፋቸውን አይተናል። በመጪው የ2018 ዓ/ም የትምህርት ዓመትም የቀድሞ ተማሪዎች ሕብረት ይህን በጎ ሥራ ለማስቀጠል ከዚህ በታች ያለውን ዕቅድ አውጥቶ በየዓመቱ የሚያደርገውን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ጀምሯል። እንዲሳተፉና ለወዳጆችዎም እንዲያጋሩ ድጋፍ በሚደረግላቸው ተማሪዎች ስም ጥሪ እናስተላልፋለን።
በዚህ ለ9ኛ ጊዜ በሚደረገው “የጣና ቤተሰብ ስኮላርሽፕ” ድጋፍ የሚከተሉትን 5 ዕቅዶች ለማከናወን ታስቧል፦

- በትምህርት ውጤትና በቤተሰብ ገቢ ሁኔታ የተመረጡ 36 ተማሪዎችን በወጪ ማገዝ። ይህም ማለት ለእያንዳንዳቸው ከመስከረም እስከ ሰኔ በወር 1000 ብር መደጎም። ለዚህ ተግባር የሚያስፈልገው ወጪ፦ 10 ወር × 36 ተማሪዎች × 1000ብር=360,000 ብር ይሆናል።
- እገዛ ለሚያስፈልጋቸው 800 ሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ (Sanitary Pads) ለአንድ ዓመት ማቅረብ። ለዚህ ተግባር የሚያስፈልገው ወጪ 300,000 ብር ይሆናል።
- ለ5 ዓይነ ስዉራን ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚረዳ የድምፅ መቅጃ መሳሪያ መግዛት። ለዚህ ተግባር የሚያስፈልገው ወጪ 35,000 ብር ይሆናል።
- ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ለሚገቡ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጊያና እና ለጣና ቤተሰብ ስኮላርሺፕ ተማሪዎች ህክምና መጠባበቂያ በጀት ማቅረብ። ለዚህ ተግባር የታቀደው የብር መጠን 150,000 ብር ይሆናል።
- የህብረቱን ስራዎች ባህር ዳር ላይ ለሚሰራ ጸሐፊ የዓመት ደሞዝ ማቅረብ። ለዚህ የሚያስፈልገው ወጪከመስከረም እስከ ነሐሴ 4000 ብር ×12 ወር= 48,000 ብር ይሆናል።
በድምሩ 893,000 ብር የሚገመት ወጪ በማድረግ እነዚህን ሥራዎች ለማሳካት ታቅዷል፡፡ እስካሁን ባለፉት 8 ዙሮች የነበረው የተማሪዎች እገዛ የተሳካው ይህን በጎ ሥራ የሰሙና የወደዱ ሁሉ ባደረጉት ያላሰለሰ የገንዘብ፣ የሃሳብ እንዲሁም የጉልበት ድጋፍ ነው፡፡

