- ዓላማ
ሴቶችን በንጽህና መጠበቂያ (Sanitary Pads) የመደገፍ ሃሳብ የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት አንዱ አጀንዳ ሲሆን ዓላማውም የንጽህና መጠበቂያ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ (9ኛ-12ኛ) ክፍል ለሚማሩ የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ት.ቤት ሴት ተማሪዎች እገዛ ለማድረግ ታስቦ የተጀመረ ነው፡፡ - የገንዘብ መጠን፤ የተማሪዎች ብዛትና የሚያጠቃልለው ጊዜ
በየአመቱ ሰማንያ አምስት ሺህ ብር (85,000) በጎ ፈቃደኛ ከሆኑ የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች መዋጮ እንደሚገኝ ታውቋል። ይህም ሁለት መቶ ሃምሳ (250) ለሚሆኑ ሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያስችል ታምኖበታል። ድጋፉ የሚደረግበት ጊዜ ከመስከረም እስከ ሰኔ ማለትም ለአንድ ዓመት ይሆናል፡፡ - መስፈርት
የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ የሚከተሉትን ሁለት መስፈርቶች መሰረት ያደረገ ነው፦
1. በአቅም ማነስ የንጽህና መጠበቂያ ለመግዛት የማይችሉ ሴት ተማሪዎች። እነዚህ ተማሪዎች ለዚህ ዓላማ በተመረጡ የትምህርት ቤቱ ሴት መምህራን፤ የሴቶች ክበብ፤ እንዲሁም እንደአስፈላጊነቱ የክፍል ስም ጠሪ መምህራንን በማቀናጀት ይመረጣሉ። በጣና ቤተሰብ ስኮላርሽፕ (Tana Family Scholarship) የተጠቃለሉ ሴት ተማሪዎች ለዚህ አድል በእጩነት አይቀርቡም።
2. በድንገተኛ ክስተት ማንኛውም የት/ቤቱ ሴት መምህር፣ ተማሪ፣ ወይም ሰራተኛ የንጽህና መጠበቂያ ቢያስፈልጋቸው ለድንገተኛ አገልግሎት ከሚቀመጥ የንጽህና መጠበቂያ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። - የአተገባበሩ ሁኔታ
በየዓመቱ በአቅም ማነስ ምክንያት የንጽህና መጠበቂያቸውን መግዛት የማይችሉ ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ በተወከሉ ሴት መምህራን፤ የሴቶች ክበብ አስተባባሪዎች እና የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት ተወካይ ጋር በመሆን በመመካከር የሚሰራ ይሆናል፡፡
ድጋፉን የሚያገኙ ተማሪዎች ስም ዝርዝር ከታወቀ በኋላ ሃላፊነቱን የሚወስደው መምህር የሴቶች ክለብ ተጠሪ ጋር በመሆን ለተማሪዎች መለያ ቁጥር በመስጠት የአተገባበሩ ሁኔታ እንዲቀል ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ - የአሰጣጥ ሁኔታ
ለአሠራር እንዲመች የተመረጡት 250 ሴት ተማሪዎች ከኮሚቴው የተሰጣቸውን መለያ ቁጥር በመያዝ በሦስት ወር አንድ ጊዜ እየፈረሙ የንጽህና መጠበቂያውን እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡
በአንድ ቀን ውስጥ 250 ተማሪዎችን ማስተናገዱ አስቸጋሪ ስለሚሆን በሁለት ቀናት በመክፈል ተማሪዎች በተመደበላቸው ቀን በመሄድ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ - የዕቃ አቅርቦትና ግዥ ሁኔታ
ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር በመነጋገር በቂ የማስቀመጫ ቦታ ከተገኘ ግዥው በአመት አንዴ ይካሄዳል፡፡
በቀድሞ ተማሪዎች ተወካይ አማካኝነት ግዥው ተከናውኖ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተርና ተወካይ በተገኙበት ለማስቀመጥ በተመረጠው ስፍራ ይቀመጣል፡፡
በየሦስት ወሩ ፈርሞ በማውጣት የአስተባባሪ ኮሚቴዎች በተስማሙት መሰረት ለተመረጡት ተጠቃሚ ሴት ተማሪዎች እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ - የመዝገብ አቀማመጥ
የተማሪዎችን ሥም ዝርዝር እንዲሁም በሚወስዱበት ጊዜ የሚፈርሙበትን ወረቀት በማዘጋጀት የበጎ ተግባሩ ተሳታፊዎች ለሆኑት (የገንዘብ ድጋፍ) ላደረጉ ሠዎች እንዲሁም ለጠቅላላ ኮሚቴው ለማቅረብ እንዲመች በመመዝገብ በመዘክር መልክ በትምህርት ቤቱ ተጠሪ ቢሮ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡
በዓመቱ መጨረሻ ላይ ማንኛውም በዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆነ ተማሪ፤ መምህር እንዲሁም የትምህርት ቤቱ ሴት ሠራተኛ ያላቸውን አስተያየት በምናስቀምጠው የሃሳብ መስጫ ሣጥን ውስጥ ወይም ቅፅ ላይ ስም ሳይጠቅሱ ማስገባት/ መጻፍ ይቻላል፡፡ - በተጨማሪ
ማንኛውም ሴት ተማሪም ሆነ የትምህርት ቤቱ ሠራተኛ በድንገተኛ ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችል በፍሬ (ብትን) የሚቀመጥ የንጽህና መጠበቂያ በትምህርት ቤቱ ውስጥ አንድ አመቺ ቦታ ተመርጦ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ - ማሳሰቢያ
ይህ ሰነድ እንደ አስፈላጊነቱ በህብረቱ ኮሚቴ በየዓመቱ የሚሻሻል ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ ይደረግ፡፡
ተማሪዎቹንና ትቤቱን ለመደገፍ ሁላችንም አብረን እንደምንቆም በሙሉ ልባችን እንተማመናለን። ቀና ተሳትፏችሁን በቋሚነት ለመቀጠል በድረገፃችን ላይ የሚገኘውን የአባልነት ፎርም እንድትሞሉም እንጋብዛለን፡፡(https://tanahaikbdr.com/contacts/)
ከአክብሮት ጋር!
የህብረቱ አስተባባሪዎች! https://tanahaikbdr.com/about/
Please feel free to send us your comment and feedback to tanagraduates@gmail.com.