የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ሕብረት የጣና ሐይቅ 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት ጉብኝት

የህብረቱ አመራሮች በቀን ሚያዚያ 18, 2015 ዓ/ም የጣና ሐይቅ ት/ቤትን የጎበኙ ሲሆን፣ በዚህ ጉብኝታቸውም፣ በህብረቱ አስተባባሪነት በት/ቤቱ የተሰሩ ስራዎችን ማለትም :-

– ኔትወርክና ኤሌክትሪክ ዝርጋታ የተሰራላቸውን የኮምፒውተር ላብራቶሪዎችን፣

– የሴት ተማሪዎች መፀዳጃ ቤት እድሳት፣

የመምህራን ማረፊያ ክፍል እድሳት እና የ17 ሎከር ስራዎች፣

– የግቢው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ የማስተካካያ ስራና

– የህብረቱን ቢሮ እድሳት ይገኙበታል።

ከጉብኝቱ በተጨምሪ ከት/ቤቱ አመራሮች ጋር ስለተሰሩት ስራዎችና ወደፊት ሊሰሩ ስለሚችሉ ስራዎች የተወያዩ ሲሆን የት/ቤቱ አመራሮች ስለተሰራው ስራ አመስግነው ብዙ የት/ቤቱን ጥያቄዎች እንደመለሰላቸው ገልጸዋል። ስራዎች በጊዜ እንዲያልቁ ህብረቱ ያከናወነውን የክትትል ስራም አድንቀዋል።

በተለየ መልኩ ህብረቱ በተማሪዎች ላይ እየሰራ ስላለው ነገርም ማለትም ከ10ኛ-12ኛ ክፍልና ወደ ዩኒቨርስቲ ለሚገቡ ለ32 ተማሪዎች፣ አመቱን ሙሉ (700 ብር በወር) የሚደረገው ድጋፍ፣ ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ አግኝተው ጥሩ ውጤት ላመጡ 17 ተማሪዎች (በግለሰብ 3000 ብር) ማበረታቻ ለመጓጓዣ ድጋፍ መደረጉን አድንቀዋል።

ለሌሎች ተማሪዎች የተሻለ እንዲሰሩ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። ሌላው የተገለጠው ነገር ፣ የሴቶች የንህጽና መጠበቂያ ድጋፍ ነው። ይህ ድጋፍ ከ350 በላይ ለሚሆኑ ሴት ተማሪዎች ለአመት የሚሆን ድጋፍ የተደረገበት ነው። እንዲሁም ለአስቸኳይ የሚሆን ለት/ቤቱ ሴት ሰራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል። እንዲሁም ለ6 አይነስውራን ተማሪዎች የመቅረጸ ድምጽ ድጋፍ እንደተደረገ በውይይቱ ላይ ተገልጧል።

በተጨማሪም ምንም እንኳን እኒህ ስራዎች ቢሰሩም ት/ቤቱ አሁንም ብዙ ችግሮች እንዳሉበትና የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰሩ የሚገባቸው ለምሳሌ የወንድና ሴት መፀዳጃ ቤት ስራ፣ የሴት ተማሪዎች የንህጽና መገልገያ መቀየሪያ ክፍል ስራ (ክፍሉ አለ ክፍፍልና የተወሰነ እድሳት የሚፈልግ)፣ የኬሚስትሪና ፊዚክስ ላብራቶሪዎች ጠረንጴዛዎች፣ የዲጅታል ላይበራሪ የኔትወርክ አቅም ማሳደግና የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል።

በህብረቱ አመራሮች በኩል፣ የት/ቤቱ አመራሮች የታቀዱ ስራዎችን እንዲሰሩ ለሚያደርጉት ትብብር ያመሰገኑ ሲሆን፣ ወደፊትም ይህ ትብብር እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልጠዋል።

ከህብረቱ አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ ሰሎሞን ኑርጋ ባነሱት ሃሳብ፣ የህብረቱ ዋና ስራ ተማሪዎች ላይ መስራት ሲሆን፣ ነገር ግን ውጤታማ ተማሪ ለማግኘት ምቹ ከባቢን መፍጠር ዋና አጋዥ በመሆኑ ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል። በተጨማሪም የት/ቤቱ አመራር ቀድሞ እያቀደ ተነሳሽነቱን የሚወስድ ከሆነ አባላቶቻቸውን አስተባብረው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጠዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ተሠራ፣ የህብረቱ ሰብሳቢ እንደገለጡት፣ ሁልጊዜ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ስራዎች የሚያስፈልገው ዝርዝር ስራና ዋጋ ቢቀርብ ለማገዝ እንደሚመች በተለይ የሴቶች የንህጽና መቀየሪያ ቦታ እድሳት ዋጋው በቶሎ ተሰርቶ ቢቀርብ ለአጋሮቻቸው በመንገር ማስፈጸም እንደሚቻል ገልጠዋል።

አቶ ምኑየለት ጌትነት ፣ ሌላው አመራር፣ ት/ቤቱን የተሻለ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ህብረቱ የሚችለውን እንደሚያደርግ ገልጠው ለት/ቤት አመራር ለሚያደርጉት ትብብር አመስግነዋል።

በመጨረሻም የተሰሩ ስራዎችን በመጎብኘት በት/ቤት የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀዋል።

comment