THAN Coordinators School Visit
Tana Haik Alumni Network coordinators visited the school and met Tana Family Scholarship winner students. Voice recorders donated by THAN members delivered to sight impaired students.
Below is the report from Amhara Mass Media Agency
“ባሕር ዳር፡ መስከረም 5/2012 ዓ.ም (አብመድ) የዐይነ ስውራንን አቅም ለመጠቀም ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚያስፈልግ የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረት አሳሰበ፡፡
ኅብረቱ ለትምህርት ቤቱ ከሚሰጠው ሁለንተናዊ ድጋፍ ባሻገር ዛሬ ለዐይነ ስውራን የትምህርት አቀባበል ምቹ ማድረጊያ መቅረፀ ድምፅ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የጣና ሐይቅ ሁለተኛና ከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ ስመኮነ መላክ የዓለምን ፈተና ለማሸነፍ መማር ብቻ ሳይሆን በእውቀት ተፎካካሪ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ስለተደረገለት ድጋፍ ሲናገርም “የምንማረው ራሳችንን ለመቻል ብቻ ሳይሆን እንዲህ ሆኖ ላስተማረው ወገናችን የምንችለውን ለማድረግ ነው፤ ዐይነ ስውር ሆኜ፣ ማየት ከሚችሉ ተማሪዎች ጋር ስማር መምህራን እያስተማሩ ማስታወሻ ማስቀረት አልችልም፤ የተማርሁትን እንኳን እንደገና አንብቦ ለመረዳት የግድ አንድ ሰው ያስፈልገኝ ነበር፤ እነዚህ ሁሉ መሰናክሎች እያሉ ዛሬ 12ኛ ክፍል ደርሻለሁ” ብሏል ተማሪው የሁኔታውን አስቸጋሪነት ሲያስረዳ፡፡
ከቀድሞ የጣና ሐይቅ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለችግሩ መፍትሔ ሊሆን የሚችል ዘመናዊ መቅረፀ ድምፅ በመቀበሉ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን ዕድል ማግኘቱን ነው የተናገረው፡፡ ከዚህ በፊት በውስንነት ያነሳቸው የነበሩ ምክንያቶችንም እንደሚያስቀርለት ተማምኗል፡፡ ተጨማሪ መጽሐፍትን በመቅረጸ ድምፁ በማስነበብ፣ መምህራኑ ሲያስተምሩም ድምጻቸውን በመቅዳት የነበሩበትን ችግሮች እንደሚፈታ ተስፋ አድርጓል ተማሪ ስመኮነ፡፡ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ኅብረት ያደረገው አርዓያነት ያለው ተግባር የማኅበረሰብ ግንባታ ላይ የራሱን ከፍተኛ እገዛ ስለሚያደርግ ሌሎችም ሊማሩበት የሚገባ በጎ ተግባር እንደሆነም ነው አስተያዬት የሰጠው፡፡
የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረት የአዲስ አበባ አስተባባሪ ወይዘሪት ራሔል ወንዴ ኅብረቱ ለዐይነ ስውራን ተማሪዎች ድጋፍ ያደረገው በትምህርት ሂደቱ እየደረሰባቸው ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በማሰብ እንደሆነ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በትምህርት ቤቱ እየተማሩ ለሚገኙ 30 ዐይነ ስውራን መቅረፀ ድምፆችን መስጠታቸውን ነው የገለጹት፡፡ ኅብረቱ ከዚህ በፊት በራሳቸው አቅም መማር ለማይችሉ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል የመፍጠር፣ ለሴቶች የንፅህና መጠበቂያ የማከፋፈል፣ የቤተ መጽሐፍት እድሳት እና የመጽሐፍት ድጋፍ ማድረጉንም ወይዘሪት ራሔል አስታውቀዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም ኅብረቱ የትምህርት ቤቱን የውሃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ዕቅድ ይዞ እየሠራ እንደሆነም ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ”
Tana Haik Alumni Network
You can also find information here
Social media page – THAN facebook page
Youtube channel – THAN Youtube channel