በቀድሞ የጣና ሐይቅ ምሩቃን ህብረት የተዘጋጀ
2. መግቢያ
2.1 ጣና ሃይቅ አጠቃላይ ት/ቤት
2.1.1 ስለ ት/ቤቱ
የጣና ሃይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በ1958 ዓም በባህር ዳር ከተማ ተመሰረተ። ት/ቤቱ ላባህርዳርና ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቸኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመሆን አገልግሏል። ት/ቤቱ የዕውቀት ጮራ በመፈንጠቅ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት ሰጥቷል። ከመቋቋሙ በፊት የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተማሪዎች ማደሪያ በመሆን አገልግሎት ሰጥቷል። እስከ ቅርብ ጌዜ ድረስ ጣና ሃይቅ ት/ቤት በባህርዳር ከተማ ክሚገኙት ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች መካከል አንዱ ነው። ት/ቤቱ በአሁኑ ወቅት ከ9-12ኛ ክፍል ተማሪዎችን እየተቀበለ የኮሌጅ መሰናዶ ዝግጅት በማስተማር ላይ ይገኛል።
2.1.2 የት/ቤቱ ስነ ህዝብ (ዴሞግራፊ)
በአሁኑ ወቅት የጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት 2710 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ 49.7% (1,348) ወንድ፤ የተቀሩት 50.3% (1,362) ደግሞ ሴቶች ናቸው።
2.2 የጣና ሀይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት
የጣና ሀይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት ጥቂት የጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎችና ወዳጆችን በመሰባሰብ በ2004 ዓ.ም. ተቋቋመ። ህብረቱ በዋነኝነት የጣና ሀይቅ ት/ቤትንና የት/ቤቱ ማህበረሰብን በተለያየ መንገድ ማገዝን ዓላማ ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሃገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ሃገር የሚኖሩ በርካታ አባላት አሉት።
ህብረቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ለት/ቤቱ ካደረጋቸው ድጋፎች መካከል የሚከተሉት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፤
- ለየት/ቤቱ ቤተ-መጻህፍት ወንበሮችና ጠረጴዛዎችን ገዝቶ ማስረከብና የቤተ-መጻህፍቱን አቅም ማጠናከር
- በየዓመቱ በትምህርታቸው ብልጫ ያመጡ ተማሪዎችን መሸለም
- ለት/ቤቱ መምህራንና የቀድሞ መምህራን የምስጋና የዕራት ግብዣ ማዘጋጀት
- የት/ቤቱ ቤተ-መጻህፍት በኢንተርኔት ማጠናከር
- ለት/ቤቱ የመጻህፍት ድጋፍ መስጠት
- የቀድሞ ተማሪዎች ለት/ቤቱ ማህበረሰብ አነቃቂ ንግግሮች በማድረግ ተማሪዎችን ለበለጠ ውጤት የማነቃቃት ስራ ይገኙበታል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የጣና ሀይቅ ቤተሰብ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሽፕ) በማቋቋም ጠንካራ ስራዎችን ለመስራት አቅዷል። የትምህርት ዕድሉ ተማሪዎችን የበለጠ በማገዝ በወጤታቸው ተፎካካሪ የሆኑ ዜጎችን ለመፍጠርና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ወይም በቢዝነስና በተዛማጅ የትምህርት ዘርፎች አጉሊ ውጤት የሚያስመዘግቡ ወጣቶችን ለማፍራት ያለመ ነው።
3. አላማ
በጣና ሃይቅ የት/ቤት ውስጥ የተሻለ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን የትምህርት ቁሳቁስና የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ።
በባህር ዳር ከተማ የግል ትምህርት ቤቶች መበራከት ምክንያት በመንግስት ት/ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በአብዛኛው ከአነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰብ የሚመጡ ሲሆኑ የጣና ሃይቅ ተማሪዎችም ከነዚህ መካከል ናቸው። ስለዚህ ተማሪዎች ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው። ለምሳሌ፥ የቤት ክራይ፤ የትራንስፖርት ወጪ፤ የት/ቤት መሳሪያወች እጥረት፤ ይገኙበታል። ይህንን ግምት ውስት በማስገባት በዚህ አንጋፋ ት/ቤት ለሚማሩ 24 ተማሪወች የትምህርት ዕድል (ስኮላርሽፕ) በማዘጋጀት በትምህርታቸው እንዲተጉ ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች ተማሪዎችም ለበለጠ ውጤት አንዲበረታቱ የሚያደርግ አላማ አለው።
4. ሽልማት
4.1 የስኮላርሽፕ አሸናፊዎች
በአመት ውስጥ በጠቅላላው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ከአያንዳንዱ ክፍል (Grade) ስድስት ስድስት ተማሪዎች ተመርጠው በጠቅላላው 24 ተማሪዎች ስድስት ትጠቃሚ ይሆናሉ። ከየክፍሉ ከሚመረጡት 6ቱ መካከል 3 ተማሪዎች በአጠቃላይ በትምህርት ዓመቱ ከፍተኛ ነጥብ ያላቸው ይሆናሉ። ቀሪወቹ 12 ተማሪዎች በክፍል 5፥1 የተጠቀሰውን መስፈርት የሚያሟሉ ፣ በአስተባባሪ ኮሚቴው የተመረጡ ተማሪዎች ይሆናሉ።
በተጨማሪም የጣና ቤተሰብ ስኮላርሽፕ ለሴት ተማሪዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለሴቶችን ተሳትፍ ለማሳደግ ይሰራል። ስለሆነም፦
- መስፈርት ለሚያሟሉ ሴት ተማሪዎች የስኮላርሽፑን ቁጥር መጨመር፤
- ከሚያገኙት ስኮላርሽፕ በተጨማሪ ተያያዥነት ያላቸውን ድጋፍ ማድረግ ለምሳሌ፣ የምክር አገልግሎት እና የማጠናከሪያ ትምህርት፤
- የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በጾታቸው ምክንያት የሚደርስባጨውን ማህበረሰባዊ ጫና ለመቀነስ ፣ የተለያዪ የንጽህና መጠበቂያ አቃዎችን በማቅረብና አስፈላጊ ሆነው በሚገኙ ድጋፎችን ለማድረግ ይሰራል።
4.2 ስኮላርሽፑ የሚሰጥበት ጊዜ
ስኮላርሽፑ የሚሰጠው ለአንድ የትምህርት ዓመት ሲሆን ድጋፉ የሚደረገው በገንዘብና በትምህርት መርጃ መሳሪያዋች ይሆናል። ይሁንና ለአስተዳደር ዓመች እንዲሆን በማሰብ የስኮላርሽፕ አሸናፊ ተማሪዎች የሚደረግላቸው ድጋፍ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሆናል ።
4.3 ስኮላርሽፑ የሚሰጥበት መንገድ
የጣና ቤተሰብ ስኮላርሽፕ ድጋፉ የሚያደርገው በገንዘብና በትምህርት መርጃ መሳሪያዋች ይሆናል። ነገር ግን የሚሰጠው የድጋፉ መጠን የሚወሰነው በሚገኘው የመዋጮ ገንዘብና እንደ ተማሪው የሚያስፈልገው የእርዳታ ዓይነት ሊለያይ ይችላል ።
በተጨማሪም እርዳታ የሚሰጥበት ዓይነትና መጠን የጣና ቤተሰብ ስኮላርሽፕ አባላት ሃሳብ ቀርቦበት ከጸደቀ በኋላ ተፈፃሚ ይሆናል ።
5. የትምህርት ዕድል (ስኮላርሽፕ) ማመልከቻ
5.1 መስፈርት
ሁሉም የጣና ሀይቅ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመማር ላይ ያሉ ከ9-12 ክፍል ተማሪዎች ለዚህ የትምህርት ዕድል ማመልከት ይችላሉ። አመልካቾች የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟለት ይጠበቅባቸዋል፤
- አመልካቾች በመማር ላይ ያሉ ከ9-12 ክፍል የቀን ተማሪዎች መሆን አለባቸው፤
- አመልካች ተማሪዎች የቀድሞ አመት ውጤታቸው ከ85% በላይ አማካይ መሆን አለበት።
5.2 መሟላት ያለባቸው የማመልከቻ ዶክሜንት
ማንኛውም አመልካች ተማሪ የሚከተሉትን ዶክሜንቶች ማሟላት ይጠበቅበታል፤
- የት/ቤት የተማሪ መታወቂያ ኮፒ
- የተማሪው የቀድሞው ዓመት የትምህርት መረጃ (ትራንስክርቢት)ኮፒ
- የተሞላ የትምህርት ዕድል ማመልከቻ ፎርም
የአመልካች ተማሪዎች የቤተሰብ መረጃ በማመልከቻ ፎርሙ ላይ የሚሰፍርበት ምክንያት መረጃው ለውስጥ አገልግሎት ለመጠቀም ብቻ ነው። ቤተሰብ መረጃ እንደ መስፈርት አያገለግልም።
5.3. ማመልከቻ ማቅረቢያ እና መጠናቀቂያ ጊዜ
በየዓመቱ የትምህርት ዓመቱ ከማለቁ በፊት ተማሪዎች የስኮላርሽፕ ማመልከቻ ፎርም ሞልተው የሚያቀርቡበት ቀናት በግልጽ በጣና ሀይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት አማከኝነት በማስታወቂያ ይፋ ይደረጋል። ማስታወቂያውም የማመልከቻ መስፈርቱን እንዲሁም የማመልከቻ ቦታና ቀን በግልጽ የሚያሳይ ይሆናል።
5.4.ማመልከቻ ማስረከቢያ
አመልካች ተማሪዎች ማመልከቻቸውን በባሀርዳር ከተማ የማህበሩ ተወካዮች ማስገባት ይችላሉ።
6. የስኮላርሽፕ አሰተዳደር እና መዋቅር
6.1 የስኮላርሽፕ አሰተዳደር ኮሚቴ
የጣና ቤተሰብ ስኮላርሽፕ አሰተዳደር ኮሚቴ በየዓመቱ በሚከሄድ ጠቅላላ ጉባዔ ይመረጣል። የስኮላርሽፕ አሰተዳደር ኮሚቴው የሚከተሉትን አባላት የያዘ ይሆናል፤
- ሶሰት በባህርዳር የሚኖሩ የቀድሞ ተማሪዎች ተወካዮች፤
- አምስት በውጭ ሃገር የሚኖሩ የቀድሞ ተማሪዎች ተወካዮች፤
- ሁለት የትምህርት ቤቱ አስተማሪዎች (አስተዳደር ሰራተኞች)ን የያዘ ይሆናል።
6.2 የአስተዳደር ኮሚቴው ሃላፊነት
- የአመልካች ተማሪዎችን መርሃግብር ማውጣት እና ማሳወቅ፤
- ማመልከቻዎችን ማሰባሰብ እና ማስተባበር፤
- ማመልከቻዎችን ማጣራት እና ወጤት ማሳወቅ፤
- የተማሪዎችን ውጤት ማመሳከርና ከአስተማሪዎች ወይም ከት/ቤት አስተዳደረ ጋር ግምገማዎችን መቀበል፤
- የውጤት መግለጫ ጊዜውን በአመት አንድ መወሰን ጊዜ መወሰን፤
- የአመቱን የሽልማት በጀት ማቀድና ለህብረቱ በጀት መወሰን፤
- በአመት ሁለት ግዜ ሪፖርት ማሳወቅ እና እቅዶችን ነድፎ በጠቅላላ ጉባኤው ማስፀደቅ፤
- ሽልማቱ በአመት ሁለት ጊዜ እንዲሰጥ ማድረግ፤
- የአመቱን የብቃት መመዛኛ ሪፖርት ማዛጋጀትና ለህብረቱ እንዲሁም ለት/ቤቱ አስተዳደር ማቅረብ። ሪፓርቱ የገንዘብና የአፈጻጻም ሁኔታዎቹን የሚያካትት ሲሆን የወደፊት እርማቶቹን የያዘ ሊሆን ይገባል።
የስኮላሽፕ ኮሚቴ ለተሸላሚዎች ሽልማቱን የሚሰጥበትን መንገድ እንደአመቺነቱ ሊተገብረው ይችላል። የገንዘብ ሽልማቱ በአመት ሁለት ጊዜ በአሸናፊዎች የባንክ ሂሳባቸው ውስጥ ገቢ ይሆናል። ቢቻል የመንፈቀ አመቱ ትምህርት ከመጀመሩ ከሁለት እስከ አራት ሳምንት ቀድሞ ይሰጣል።
7. የግምገማ ሂደት
የአስተዳደር ኮሚቴው ንዑስ ክፍል 5.1ን መሰረት በማድረግ የተላኩ ማመልከቻዎችን ይገመግማል ፤ ስብሰባ በመጥራትም በማጣሪያው ያለፉ ተማሪዎችን ዝርዝር ያዘጋጃል።
8. የዕጣና ማስታዎቂያ ሂደት
ኮሚቴው የመጨረሻ አሸናፊዎችን ለመለየትና ይፋ ለማድረግ ልዩ ዝግጅት ያዘጋጃል። የመጨረሻ አሸናፊዎችን ለመለየት ሁሉም እጩ ተወዳዳሪዎች የክፍል ደረጃቸውንና ጾታቸውን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ወደ እጣ እንዲገቡ ይደረጋል። ጥሪ በተደረገላቸው እንግዶች አማካኝነትም የእጣ ማውጣት ሂደቱ ይካሄድ እና አሸናፊዎች እንዲታዎቁ ይደረጋል። በመጨረሻም ኮሚቴው የእጣ ውጤቱን መሰረት በማድረግ የመጨረሻ 24 አሸናፊዎችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደርጋል።
9. የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድ
የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት በአሁኑ ሰዓት ዋና የገቢ ምንጮቹ ከቀድሞ የት/ቤቱ ተማሪዎችና የት/ቤቱ ወዳጆች በሚገኝ ድጋፍ ሲሆን ይህንን መርሃ ግብር ለማስቀጠል ልዩ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን ያመቻቻል። ለዚህ ዓመት በእቅድ ላይ የተያዘዉን ነጻ የትምህርት እድል መርሃ ግብር ለማስቀጠል 12,000 የአሜሪካን ዶላር በጀት የተያዘ ሲሆን መርሃ ግብሩን ዳር ለማድረስ ህብረቱ ልዩ ልዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶችን መተግበርና የተለያዩ አካላትንም ማሳተፍ እንደሚገባ ያምናል። ከተለያዩ የውጭ አካላት ሊገኝ የሚችለውን ድጋፍ ለማፋጠን የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት በአሜሪካን ሃገር እንደ ተራድዖ ድርጅት ህጋዊ እውቅናን በማግኘት ተመዝግቧል።
10. ቁጥጥርና መዝገብ አያያዝ
ነጻ የትምህርት እድሉን የተመለከተ ማንኛውም ወጪ በውጭ ኦዲተር የሚፈተሽ ሲሆን ውጤቱም ሁሉም አባላት እንዲያዩት ይደረጋል።
Join Tana Haik Alumni Network :
- Viber group: https://invite.viber.com/?g=MCNz2pNfI0Y5jZVgy9VPR-lzyhXdJD2G
- https://www.facebook.com/groups/325812767871551/
- https://www.gofundme.com/TanaScholarship
Tana Haik Alumni Network