Tana Alumni Skype Meeting Report

መጋቢት 22.2005/ ማርች 31.2013

(Click here to read in PDF)

የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ከሰሜን አሜሪካና አውሮፓ በስካይፕ ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። ቤተሰባዊ ስሜት የነበረው ውይይት በሰላምታና ደህንነትን በመጠያየቅ ተጀምሯል። ዳዊት (አላባማ) ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጲያ በነበረው ቆይታ የነበረውን ስሜትና የት.ቤቱን ይዞታ አካፍሎናል። የተነሱ ጥያቄዎች ላይም በሁሉም ተሰብሳቢ ውይይት ተደርጓል። እንደአጀንዳ ከተያዙት ነጥቦች ውስጥ እነዚህን ተነጋግረናል፦

1. የላይብረሪያን ደሞዝ

በቀድሞ ተማሪዎች ስም ሥራ ለጀመረው ላይብረሪ ላይብረሪያን እንደሚያስፈልግ ከዚህ በፊት ተገልጾ ነበር (የፌቡ መልዕክት ከኢትዮጵያ)።ዳዊት በአካል ተገኝቶ ያየውን የላይብረሪውን ሁኔታ አካፍሎናል። ተወያዮቹ በደሞዝ የሚያገለግል አንድ ላይብረሪያን ለጊዜው በቂ እንደሆነ ተወያይተዋል። በትርፍ ጊዜያቸው አገልግሎቱን የሚያግዙ (የቤ.መጽሐፍት ክበብ አባል የሆኑ) ተማሪዎችን ማሳተፍ እንደ ተጨማሪ ነጥብ ተይዟል። ደሞዙን በቀጣይነት ለመሸፈን ምን መደረግ እንዳለበትም ተወያይተናል።በዓመታዊው የሰ.አሜሪካ የእግር ኳስ ፕሮግራም ላይ መገናኘትና ዓላማውን ገልፀን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ልናደርግ እንደምንችል ሀሳብ ተሰጥቷል። እንደተጨማሪ የቀድሞ ተማሪዎች ወርሀዊ መዋጮም ቢታሰብበት ለምናደርገው እገዛ ቀጣይነት ጥሩ መሆኑ ተነስቷል። ተወያዮች በተነሱ ነጥቦች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠን እንደመነሻ የሚሆን ገንዘብ ($200) ለመላክ ተስማምተናል። ስብሰባው ላይ መገኘት ላልቻሉና መሳተፍ ለሚፈልጉ የቀድሞ ተማሪዎችም በፌቡ ለማሳወቅ ተስማምተናል። ለት.ቤቱ ገቢ ማስገኛ የሚሆኑ መንገዶች ላይ አዳዲስ ሀሳቦች ተነስተው ወደፊት ይበልጥ ልንወያይ አቅደናል።

2. መጽሐፍትና ኢንተርኔት

ታናናሾቻችን ጥሩ ትምህርታዊ መረጃ የሚያገኙበት መንገድ ማመቻቸት ከተያዙት ዕቅዶች አንዱ ነው። ለዚህ የሚያስፈልጉ መጽሐፍትን እንዴት ማሰባሰብ እንደሚቻል ተወያይተናል። መጽሐፍትን አሰባስቦ በ’ኮንቴነር’ መላክ ወጪው ከፍተኛ ስለሆነ ለጊዜው መላኪያ መንገዶችን ማመቻቸት የላኪው ድርሻ ይሆናል። የኢ.አ.መንገድ በሚያደርገው የቀጥታ በረራ የሚፈቅደው የማጓጓዣ መንገድ አለ የሚል ሀሳብ ተነስቷል። ሙሉ መረጃውን ለማግኘት ዲ.ሲና አካባቢው ያሉ ተወያዮች ኃላፊነት ወስደዋል።

የኢንተርኔት መስመር በቀድሞ ተማሪዎች አማካኝነት ወደ መጀመሪያው ላይብረሪ ገብቷል። ይህንን መስመር ወደ ሁለተኛው ላይብረሪም መውሰድ እንደሚያስፈልግ ውይይቱ ላይ ተነስቷል።

3. አቅም ማሳደግ

የተማሪዎችን አቅም ለማሳደግ በቀድሞ ተማሪዎች የሚሰጥ ትምህርት (Tutorial Class) ስለማመቻቸት ተወያይተናል። እንደመነሻ ለተወሰኑ ተማሪዎች መሰረታዊ የኮምፒውተር ትምህርት መስጠት እንደሚቻል ሀሳብ ቀርቧል። እገዛው ተማሪዎቹን ወደኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የበለጠ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ውይይቱ ላይ ተነስቷል። ሀሳቡን ኢትዮጵያ ከሚገኙ የቀድሞ ተማሪዎች ጋር ለመወያየት ታቅዷል።

4. ተጨማሪ

በቅርቡ ስለነበረው የመጽሐፍት ሥጦታና ተማሪዎችን የማበረታታት ፕሮግራም ተወያይተናል። የዝግጅቱ መንፈስና ውጤቱም ጥሩ እንደነበር ተነስቷል። በቦታው ላልነበርን ተጨማሪ ፎቶዎች የፌቡ ገፁ ላይ ይለቀቃሉ።በጊዜው የታዩት መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ክፍተቶች ተነስተዋል። ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ‘ብላክቦርዶች’፣ የክፍል መስኮቶች፣ ‘ላይቲንግ’ እንደምሳሌ ተጠቅሰዋል። የታዩትን ወቅታዊ ጉድለቶች ይበልጥ ለመረዳትና ለመፍታት በጽሑፍ እንዲያዙ ታቅዷል።

በመጨረሻ ውይይቱ ወርሀዊ እንዲሆን (በወር የመጨረሻ እሁድ) ተነጋግረን ተሰነባብተናል። ለመሳተፍ ከቻሉ የጣና ቤተሰብ አባል ይሁኑ፣ ኑና ለታናናሾቻችን ስኬት አብረን እንሥራ።